Quick Links

 

 

 

 

አዲሱ የፌስቡክ የአይነስውራን ቴክኖሎጂ

 

በፌስቡክ፣ ትዊተር እና ኢንስታግራም ብቻ በየቀኑ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ምስሎች (ፎቶግራፎች) ይጫናሉ። ያም ሆኖ አይነስውራንን ብቃት ባለው መልኩ ምስሎችን እንዲገነዘቡ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አናሳ መሆናቸው ነው የሚነገረው። 

ፌስቡክ አይነስውራን ምስሎችን እንዲረዱ የሚያስችል ቴክኖሎጂን አስተዋወቀ

ይህን ለመቅረፍ በሚል ይመስላል ፌስቡክ በትናንትናው ዕለት አዲሱንና አይነስውራን ምስሎችን በሚገባ እንዲያዩ(እንዲረዱ) የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ያስተዋወቀው። አይነስውራን ቀደም ሲል ኮምፒውተርን በቀላሉ ለመጠቀም ውስብስብ እንደሆነ የተነገረለትን “ስክሪን ሪደር” የተሰኘውን መተግበሪያ ነው የሚጠቀሙት። ይህም ኮምፒውተሩ ድምፅን ጨምሮ የተለያዩ ማብራሪያዎችን የሚሰጥ ሲሆን፥ ለማንበብና ለመፃፍ የሚጠቀሙበትን ብሬልንም ያካተተ ነው። ይሁንና ይህም ቴክኖሎጂ ቢሆን ምስሎችን ለመረዳት አላስቻላቸውም።


አሁን ግን ፌስቡክ አዲስ በሚጠቀመው መተግበሪያ አማካኝነት ለሰዎች ቅርብ የሆኑና የተለመዱ 80 መጠሪያዎችን በቀላሉ እንዲረዱ እና በምናባቸው እንዲስሉ ማድረግ መቻሉን ተናግሯል። በእያንዳንዱ ምስል (ፎቶግራፍ) ስር በአማራጭነት ገላጭ ማብራሪያዎች በፅሁፍ እንዲቀመጡ መደረጉም ተመልክቷል። 

አዲሱ ቴክኖሎጂ ከሚያስተዋውቃቸውና አይነስውራኑ ከሚያነቧቸው ምስሎች መካከል፦

  • ከትራንስፖርት መገልገያዎች፦ መኪና፣ ጀልባ፣ አውሮፕላን፣ ብስክሌት፣ ባቡር፣ሞተር ብስክሌት ፣መንገድ የመሳሰሉት ይገኛሉ።
  • ከአካባቢ፦ መናፈሻ፣ ተራራ፣ ዛፍ፣ በረዶ፣ ሰማይ፣ ውቅያኖስ፣ውሃ፣ የወንዝ ዳር መዝናኛ ስፍራ (beach) ፣ የባህር ሞገድ፣ ፀሃይ፣ ሳር ወዘተ… ይጠቀሳሉ።
  • ከስፖርት፦ ቴኒስ፣ ዋና፣ ስታዲየም፣ቅርጫት ኳስ፣ ቤዝ ቦል፣ ጎልፍ፣ መረብ ኳስ ይገኙበታል።
  • ከምግብ፦ አይስ ክሬም፣ ሱሺ(የጃፓን ተወዳጅ ምግብ ነው)፣ ፒዛ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ቡና፣ ሻይ የመሳሰሉት ተዘርዝረዋል።
  • ከፊት ገፅታና አለባበስ፦ ህፃን፣መነፅር፣ጢም፣ ፈገግታ፣ ጌጣጌጥ፣ ጫማ፣ የራስ በራስ ፎቶግራፍ (selfie) እና ሌሎችም በመሳሪያው አማካኝነት አይነስውራን ይረዷቸዋል የተባሉ ነገሮች ናቸው።

ይህን ቴክኖሎጂ የቀረፀውም “ሬቲኒቲስ ፒግመንቶሳ” በተሰኘውና በአይናችን ምስል እንዲከሰት የሚያደርግው ሬቲናን በሚጎዳው ችግር ምክንያት እይታውን ያጣው የተቋሙ የኤሌክትሮኒክስ ባለሙያ ማት ኪንግ ነው።


“በፌስቡክ አብዛኛዎቹ መልዕክቶች የሚቀርቡት በምስል ነው፤ ታዲያ ይህን ምስል አይነስውራን ካላገኙ ከጨዋታው ውጪ የተደረጉና የተገለሉ አይነት ስሜት እንዲያድርባቸው ስለሚያደርግ ቴክኖሎጂውን ወሳኝ ያደርገዋል” ብሏል ማት።