Quick Links

 

 

 

 

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመለስ ነው

 

በመላ አገሪቱ የትራፊክ አደጋ ከመጠን በላይ እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት ሥራ ላይ ውሎ የነበረው የትራፊክ ደኅንነት ደንብ እንዲሻሻል ተወሰነ፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በደንቡ የመንጃ ፈቃድ አወጣጥ ሒደት ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመለስ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን፣ ረቂቅ ደንቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ታውቋል፡፡

 

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቅርቡ ሥራ ላይ ውሎ በነበረው የትራፊክ ደንብ ላይ ኅብረተሰቡ ቅሬታ እያቀረበ በመሆኑና የትራፊክ አደጋውም እየበዛ በመምጣቱ ማሻሻያ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመለስ ነው

በዚህ መሠረት ሥራ ላይ ባለው ደንብ በአንድ ጊዜ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ ድረስ መስጠት እንዲቆም፣ በምትኩ ቀድሞ እንደነበረው በልምድ ላይ የተመሠረተ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ተግባራዊ ይደረጋል በማለት አቶ ያብባል ገልጸዋል፡፡

ከትራንስፖርት ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በ2007 ዓ.ም. በአገሪቱ የ3,847 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 5,918 ሰዎች ከባድ ጉዳት፣ 6,508 ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

 

በ2008 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር ብቻ በመላ አገሪቱ የ2,978 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 4,898 ሰዎች ለከባድ አካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከ670 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት መውደሙም ተመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት በትራፊክ አደጋ የ15 ሺሕ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

 

ለዚህ የከፋ አደጋ እየቀረበ የሚገኘው ዋነኛ ምክንያት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ በመሆኑ ደንቡን ማሻሻል ይገባል ተብሏል፡፡ በዚህ መሠረት ደረቅ፣ የሕዝብና የፈሳሽ ተሽከርካሪዎችን ለማሽከርከር በየደረጃው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ እንደሚያስፈልግ በደንብ ማሻሻያው ላይ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ያብባል እንዳሉት የቀድሞ የትራፊክ ደኅንነት ደንብ የተዘጋጀው ከሌሎች አገሮች ልምድ ተወስዶ ነው፡፡ ነገር ግን ያሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ይህንን ደንብ ተግባራዊ ማድረግ ያላስቻሉ በመሆናቸው ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል፡፡

 

በአዲስ አበባ ደግሞ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ለውጥ የታየ ቢሆንም፣ እስከ ግንቦት 2008 ዓ.ም. ደረስ ግን 323 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው እንዳለፈ አቶ ያብባል አስረድተዋል፡፡ ከየካቲት 14 እስከ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ብቻ 92,706 የትራፊክ ደንብ መተላለፎች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ምንጭ፡ ethiopianreporter.com, 03 Aug, 2016