Quick Links

 

 

 

 

የአተት በሽታን ለመከላከል ትኩረት ሚሹ ጉዳዮች

 

በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በሽታው በሀዋሳ ከተማ ተከስቷል እየተባለ የሚወራው ሀሰት መሆኑን ገጸው አዲስ አበባ ሄዶ የተመለሰ አንድ ግለሰብ በዚህ በሽታ ተጠርጥሮ በአዳሬ ሆስፒታል በተዘጋጀ ጊዜያዊ የአተት በሽታ ሕክምና ማዕከል የሕክምና እርዳታ እንደተደረገለት እና ሌሎች ከአዲስ አበባ መጥተው በበሽታው የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎችም ለህክምና ወደ ማዕከሉ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከሌላ ቦታ በሚመጡ ታማሚዎች ምክንያት በሽታው በሀዋሳ ከተማ እንዳይሰራጭ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አቶ እንዳሻው አሳስበዋል፡፡ አተት በሽታ ጥንቃቄ እንዲረዳዎት የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ይበሏቸው፡፡

ምልክቶች...

ድንገት የሚጀምር መጠነ ብዙ፣ ተከታታይና አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሚከሰት ሲሆን፥ ከዚህም የተነሳ ከሰውነት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችና ፈሳሽ በብዛት ስለሚወገዱ ከፍተኛ የሰውነት ድርቀት (የአይን መሰርጐድ፣ የአፍና የምላስ መድረቅ፣ እንባ አልባ መሆን፣ የሽንት መጠን መቀነስና የቆዳ መሸብሸብ) ያስከትላል።

የመከላከያመንገዶች...

በሽታውን በቀላሉ መከላከል የሚቻል ስለሆነ ከበሽታው ራስንና ቤተሰብን ብሎም አካባቢን ለመከላከል የግልና የአካባቢዉን ንጽህና በሚገባ መጠበቅ አስፈላጊ ነው።

የበሽታው ምልክት የታየበት ሰው ከተገኘ በአስቸኳይ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም እንዲሄድና አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና ማግኘት ይኖርበታል።

እንዲሁም፦ 

• ውሃ አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠቀም

• በውሃ ማከሚያ መድሃኒት የታከመ ውሃ መጠቀም

• ምግብን በሚገባ አብስሎ በትኩስነቱ መመገብ

• የምግብ ዕቃዎች ንጽህና መጠበቅ
• መፀዳጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም

• እጅን ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብ ከማዘጋጀት በፊት፣ ምግብ ከማቅረብ በፊት፣ ምግብ ከመመገብ በፊት፣ ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ፣ ሕጻናትን ጡት ከማጥባትና ከመመገብ በፊት አንዲሁም ለበሽተኛ እንክብካቤ ካደረጉ በኋላ በሣሙና በሚገባ መታጠብ

• ማናቸውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ ውሃን እንዳይበክል በአግባቡ በተመደበለት ስፍራ ማስወገድ

• በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ

• ከበሽተኛው ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር ንክኪ ያላቸውን እቃዎችና ቦታዎችን በአግባቡ ማጽዳት፡፡

ምንጭ፡ የክልሉ ጤና ቢሮ እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት