Quick Links

 

 

 

 

400 ሺሕ ሰዎችን ለመቅጠር የሚያስችሉ ፓርኮች፣ በአማራ፣ በአሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች ሊገነቡ ነው

 

በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጋራ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ፣ ኃይሌም ይህንኑ አስረድተዋል:: በመሆኑም ለሚገነቡት የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ፕሮጀክቶች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ እየተገኘ ስለመሆኑም የጠቆሙት አቶ ታደሰ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶችን በማሳካት በቀላል ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከአሥሩ አገሮች አንዷ እንድትሆን የተወጠነ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል:: አገሪቱ ይህንን የኢንዱስትሪ ራዕይዋን ለማሳካት እያደረገች ስለምታገኘው ጥረት ለውጭ ዲፕሎማቶች በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ወቅት፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ሊያደርጓት የሚችሉ ቅድመ ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል:: ለዚህ ምሳሌ ሆኖ የቀረበው በቅርቡ የተመረቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው:: ወደ ግንባታ የገቡትም ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢንዱስትሪው ዘርፍ ሊደረስበት የታሰበውን ውጤት የሚያመለክቱ ናቸው::

 

ከመደበኞቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሻገር ግን መንግሥት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮችን ለመገንባት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ካሳወቀ ሰነባብቷል:: የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች በጥሬው ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን አቀነባብሮ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሲሆን፣ ለዚህ ሥራ አዋጭ በሆኑ አካቢዎች ላይ ለግንባታ የሚውሉ ሥፍራዎች ተለይተው የዲዛይን ሥራም መገባደዱ ተገልጿል:: ሌላኛው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስም በተለያዩ ክልሎች ይገነባሉ ተብለው ስለሚጠበቁ 14 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አብራርተዋል:: ዶ/ር መብራቱ እንደገለጹት፣ ኢንዱስትሪዎቹ የሚገነቡባቸው ቦታዎች የግብርና ውጤቶችን ለማቀነባበር ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች መገኛ አካባቢዎችን በመምረጥ ነው:: የሥጋ ማቀነባበሪያዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል:: የሰሊጥ፣ የቡና የመሳሰሉትም የማቀነባበሪያው ውጥኑ አካላት ናቸው:: ለእነዚህ ፓርኮች ግንባታ የአሜሪካው ዩኤስኤአይዲ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም (ዩኒዶ) ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ከአሥራ አራቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ውስጥ አራቱ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. ይገነባሉ ተብሏል:: ለፓርኮቹ ሙሉ የመሠረተ ልማት የሚሟላላቸው፣ ኢንቨስተሮች ማሽነሪዎቻቸውን ብቻ ይዘው በመምጣት ወዲያው ገጥመው ወደ ሥራ እንዲገቡ ዕድል የሚሰጡ ናቸው::

 

ለፓርኮቹ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች በቅርብ የሚሰጡበት ሲሆን፣ እንደ የባንክ የአገልግሎቶች ያሉት ሳይቀር በፓርኮቹ ውስጥ ይኖራሉ:: እንደ ጉምሩክ ያሉ መሥሪያ ቤቶችም በፓርኩ ውስጥ ያሉ አምራቾችን በቅርብ ለማገልገል እንዲችሉ ቢሮ ከፍተው የሚሠሩ ስለሚሆን፣ ፓርኮቹ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት መጓደል የሌለባቸው፣ ኩባንያዎቹም የሚፈልጉትን አገልግሎት በቅርብ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ዕቅዶች ተወጥነዋል:: አራቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ወደፊት ለሚገነቡት አሥር ፓርኮች በሞዴልነት ያገለግላሉ:: ኢንዱስትሪዎችን በተለየ ደረጃ ለማሳደግ ይረዳሉ የተባሉት በእነዚህ ፓርኮች ግንባታ ሒደት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የጠየቁት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ ይህንን ለማድረግ ንግድ ምክር ቤቶችም ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል:: በሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ለማልማት አለያም በግል ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ መንግሥት የተለየ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚችል ገልጸዋል:: ፓርኮቹ በዚህ መልክ መገንባታቸው በዘርፉ ወደተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመግባትና የግንባታ ቦታ ለማግኘት ይወሰድ የነበረውን ረዥምና አሰልቺ የቢሮክራሲ ሒደት በመፍታት ረገድ እንዲሁም ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ አምራቾች የማምረቻ ቦታ በፍጥነት ለማግኘት ያስችላቸዋል::

 

ከዚህ ቀደም በተደረገ ገለጻ፣ በመጀመሪያ ምዕራፍ ለሚካሄዱ ግንባታዎች መንግሥት 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ያስታወቁት ዶ/ር መብራህቱ፣ 154 ሔክታር መሬት ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ግንባታ መለየቱን ጠቅሰዋል:: በመጀመሪያው ምዕራፍ 400 ሺሕ ሰዎችን ለመቅጠር የሚያስችሉ ፓርኮች፣ በአማራ፣ በአሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች እንደሚገነቡ ሲገለጽ፣ 400 ያህል ኩባንያዎችም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ውስጥ በተለያዩ ምርቶች እንደሚሳተፉ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም:: እነዚህን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያስገኛሉ ተብሎ የሚጠበቀውን ጥቅም ውጤታማ ለማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ተቋም ለማቋቋም ታቅዷል:: እስካሁን 17 የምርት መተላለፊያ መስመሮች በአገሪቱ እንደተለዩ፣ በዚህም በሰብል፣ በቅባትና ጥራጥሬ፣ በእንስሳት ሀብት፣ በዓሣ እርባታ በአትክልትና ፍራፍሬና በመሳሰሉት ምርቶች ተለይተው የተደለደሉ አካባቢዎች መጠናታቸውንና ምርቶቹን ከገበሬው ማሳ አቅራቢያ በሚተከሉ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አማካይነት እንዲዘጋጁ የሚያስችሉ ጥናቶች መካሄዳቸው ሲገለጽ ቆይቷል:: ይሁንና መንግሥት ለሚገነባቸው ልዩ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች በጠቅላላው እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊያስወጡት እንደሚችሉ እየተነገረ ነው::

 

እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመግባት ኢንቨስት ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ኩባንያዎችን ለመሳብ ግን መንግሥትም ሆነ እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ ተቋማት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው ተብሏል:: አቶ እንዳልካቸውም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ:: ንግድ ምክር ቤታቸው በቅርቡ ወደተለያዩ አገሮች በሚያደርገው ጉዞ በዘርፉ የሚሳተፉ ኩባንያዎች የተመቻቸውን ዕድል በመግለጽ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ነው:: ለአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ቢሆን በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ እንዲሁም ቢዝነሱ ምን ያህል አማራጭ ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ግድ መሆኑን ጠቅሰዋል:: በግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሙ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን ውጣ ውረድ የሚያመላክቱ አንዳንድ መረጃዎች እንዲህ ያለውን ክፍተት እንዴት ያቃልላሉ የሚል ጥያቄ ከተሳትፊዎች ቀርቧል:: በተለይ ምቹ የቢዝነስ ድባብን በተመለከተ ኢትዮጵያ የተቀመጠችበት ደረጃ ዝቅተኛ የሚባል በመሆኑ መንግሥት ይህንን ማስተካከል አለበት ተብሏል:: በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ከመንግሥት የመጡ ኃላፊዎች መንግሥት ይህንን ክፍተት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገና በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮችን ጉዳይ የሚከታተል ዴስክ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሥር የተቋቋመ በመሆኑ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት ይቻላል የሚል ምላሽ ተሰጥቷል::

 

ምንጭ፡ ethiopianreporter፣ ረቡዕ |ሐምሌ 27 ቀን 2008