Quick Links

 

 

 

 

ከመስከረም 2009 ጀምሮ በ7.5 ሚሊየን ዶላር ሰብል የማዳቀል ስራ ሊጀመር ነው

 

ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የአምስት የሰብል አይነቶችን የማዳቀል አሠራሮችን ለማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ከመስከረም  2009  ጀምሮ  ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ  ተገለጸ ።
ቢል ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የአምስት የሰብል አይነቶችን የማዳቀል አሠራሮችን ለማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ከመስከረም  2009  ጀምሮ  ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ  ተገለጸ ። ቢልጌትስ ፋውንዴሽን ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የፈጸመው  ስምምነት እንደሚያመለክተው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ  የሚደረገው  በአጠቃላይ  በ7ነጥብ 5 ሚሊዮን  ዶላር ወጪ ሲሆን  ለአምስት ዓመታት  የሚቆይ  ይሆናል ተብሏል ።

 

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ዋቅጅራ ለዋኢማ እንደገለጹት፤ ፋውንዴሽኑና ኢንስቲትዩቱ ተባብረው ተግባራዊ በሚያደርጉት ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ሲከናወን የነበረውን የበቆሎ፣ ማሽላ፣ቦሎቄ፣ ሽምብራና ስንዴ ምርጥ ዝርያዎች የማዳቀል ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮች ለማሻሻል ታቅዷል ።በፕሮጀክቱ 15 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የግብርና ምርምር ተመራማሪዎች እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ዶክተር አዱኛ ፤ የግብርና ተመራማሪዎችን እውቀትና ክህሎትን  ከማዳበሩም  በተጨማሪም በፕሮጀክቱ  አማካኝነት የሚወጡ የግብርና  ቴክኖሎጂዎች በፈጣን ሁኔታ  ለተጠቃሚዎች  በማዳረስ  ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል ።     

 

ለምርምር የተመረጡት የሰብል ዝርያዎች የተሻለ የምግብ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረግ  የፕሮጀክቱ ትኩረት  መሆኑን ጠቁመው፤  የማዳቀል  ቴክኖሎጂውንና አሠራሩን  በማሻሻል የተሻሉ  ምርጥ  ዝርያዎችን ለተጠቃሚ  አርሶ አደሩ እንዲዳረስ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል ።ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረግ ሲጀመር በበቆሎ ሰብል የሚደረገው የማዳቀልና የምርምር ሥራውን በአገሪቱ የበቆሎ  አምራችነት በሚታወቁት የምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ትኩረት  ሠጥቶ  እንደሚሠራ  ዶክተር አዱኛ  አመልክተዋል ።

 

በተጨማሪም  የሽንብራ ምርምርና የማዳቀል ሥራ  በቱሉ ቦሎ አካባቢ ፣ የማሽላ ሰብል  ምርምርና  የማዳቀል ሥራውን  በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፤ ቦሎቄን  በአገሪቱ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች እንዲሁም የስንዴ  ምርምርን  በአርሲና በባሌ አካባቢዎች በማተኮር ተግባራዊ ለማድረግ  መታቀዱን ዶክተር አዱኛ አብራርተዋል ።የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከተለያዩ የውጭ  የግብርና ምርምር አካላት ጋር  በመሆን  በሰብል ምርምር  ብቻ  60 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።

Source: http://www.waltainfo.com/news/editors_pick/detail?cid=56