Quick Links

 

 

 

 

Economic Activities in Hawassa

 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተያዘው 2009 በጀት ዓመት 18.8 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ብድር ለመስጠት አቀደ:: ከዚህ ውስጥ 11.08 ቢሊዮን ብር ብድር በበጀት ዓመቱ ውስጥ እንደሚለቀቅ ተጠቁሟል:: ባንኩ ከዚህ ቀደም ካበደረው ብድር ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብና 654.04 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት መታቀዱን ከባንኩ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል:: በተለይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አራት ቢሊዮን ብር ለሊዝ ፋይናንስ ተበዳሪዎች ቢያቀርብም፣ ተበዳሪ ሳይቀርብ በመቅረቱ ዕቅዱ ብዙም ውጤታማ እንዳልነበር ተገልጾ ነበር::

 

በዚህ ዓመት ግን ባንኩ በመላ አገሪቱ ተጨማሪ 75 ቅርንጫፎችን በመክፈቱና በሰው ኃይልም ተሟልቶ በመደራጀቱ፣ ከዚህ ባሻገርም የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ድርጅቶችን የሚመሩ ተቋማት ለተበዳሪ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠናዎችን በመስጠታቸው፣ ባንኩ ለሊዝ ፋይናንስ ተበዳሪዎች አሥር ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ማቀዱ ታውቋል:: የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ /የሊዝ ፋይናንስ/ አገልግሎት እንዲሰጥ ከመንግሥት ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: በዚህ መሠረት ባንኩ ወደ አገር የሚይገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለሚሠሩ፣ ወደ ውጭ አገሮች ምርቶች ለሚልኩና ዋስትና ማስያዝ ባለመቻላቸው የፋይናንስ ድጋፍ ላጡ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለማቅረብ አቅዷል::

 

ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ ፕሮግራም ብድር የሚሰጥበት ከፍተኛው የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ/ ሊዝ ዋጋ 80 በመቶና በኢንተርፕራይዞች 20 በመቶ የሚሸፈን ይሆናል ተብሏል:: የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2008 በጀት ዓመት 14.82 ቢሊዮን ብር ብድር ለመፍቀድ አቅዶ፣ 11.84 ቢሊዮን ብር መፍቀዱን አስታውቋል:: ከዚህ ውስጥ 6.33 ቢሊዮን ብር ለተበዳሪዎች የለቀቀ ሲሆን፣ ካበደረው ብድር 4.10 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል::

 

Source: Ethiopian Reporter , ረቡዕ |ጳጉሜን 2 ቀን 2008