Quick Links

 

 

 

 

ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በአዲሱ ዓመት የማስትሬት ፕሮግራሞችን ሊያስተዋውቅ ነው

 

 

Aviation

እስካሁን በበረራ መስተንግዶ (ሆስተስ)፣ በፍሮንት ኦፊስ ኦፕሬሽን፣ በቲኬቲንግና በሪዘርቬሽን፣ በሆቴል ኦፕሬሽን፣ በኤርላይን ደንበኞች አያያዝ ዘርፎችና በሌሎችም ተያያዥ የአቪዬሽን ሙያዎች ተማሪዎችን ሲያሠለጥን ቆይቷል:: ከዚህ በላይ ወደፊት የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎችን (ኮሜርሺያል ፓይለትስ) ለማሠልጠን የሚያስችሉትን መዋቅሮች በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝና፣ ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት ሥልጠናውን መስጠት ሊጀምር እንደሚችል አቶ ገዛኸኝ ብሩ፣ የናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ዲን ለሪፖርተር ገለጸዋል:: የናሽናል አየር መንገድ አካል የሆነው ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በአቪዬሽን መስክ በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስኮች የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን እያሠለጠነ ቆይቷል::

 

ሰሞኑን ለሦስተኛ ጊዜ በልዩ ልዩ የአቪዬሽን መስክ 285 ሠልጣኞችን አስመርቋል:: ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት፣ 285 ተማሪዎች በዲፕሎማ ደረጃ ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) ጋር በመተባበር የተሰጣቸውን ሥልጠና በማኅበሩ መሥፈርት ተፈትነው ከ90 በመቶው በላይ ዝቅተኛውን መሥፈርት በማሟላት በማለፋቸው መመረቃቸውን አቶ ገዛኸኝ አብራርተዋል:: ከዓለም አቀፉ ማኅበር በተጓዳኝ የእንግሊዙ ኢንስቲትዩት ኦፍ ማኔጅመንት ጋር በመሆን ሥልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኘው ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ፣ በዚህ ዓመት ሁለት አዳዲስ የማስትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን እንደሚያስተዋውቅ አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል::

 

ኬንያ ከሚገኘውና ከነባሩ ሞይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰጡት ኮርሶች ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት እንዲሁም አቪዬሽን ማኔጅመንት የተባሉ ሲሆኑ፣ ሁለቱም በማስትሬት ዲግሪ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠት የሚጀመርባቸው የትምህርት ዘርፎች መሆናቸው ተገልጿል:: ኮሌጁ እስካሁን በሆቴል ማኔጅመንት እንዲሁም በቱሪዝም ማኔጅመንት መስክ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል:: ምንም እንኳ በዚህ ዓመት እንደማይጀምር የታወቀው የአብራሪዎች ሥልጠና፣ ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት ሊጀመር እንደሚችል ከአቶ ገዛኸኝ ለመረዳት ተችሏል:: ከዚህ ባሻገር ግን በአቪዬሽን ሳይንስ፣ በአውሮፕላን ዲዛይን፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በኤሮናውቲካል ኢንጂነሪንግ እንዲሁም በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ መስኮች በቅድመና በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ሥልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ኮሌጁ ይፋ አድርጓል::