የቡና ጠባይን እንደ ምሳሌ

የቡና ጠባይን እንደ ምሳሌ

 

 የቡና ጠባይን እንደ ምሳሌ

 

የትውልድ ስፍራው ኢትዮጵያ በብዙዎች ዘንድ አረንጓዴ ወርቅ ተብሎ የሚጠራው ቡና ከ3 ቢሊዮን  ህዝብ እና በዓመት 500 ቢሊዮን በላይ ስኒ በመላው ዓለም ይጠጣል፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ በመብቀል (70 በላይ) ለአገሮች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ቡና ከችግኝነቱ አንስቶ ቡና ሆኖ አገልግሎት ላይ እስኪውል ድረስ የእራሱ የሆኑ ልዩ ልዩ ጠባዮች አሉት፡፡ ለዛሬ ይህን ርዕስ የመረጥኩት ስለ ቡና ጠቀሜታ ለማውራት ሳይሆን ጠባዩን በምሳሌነት በመውሰድ ከሰው ህይወት ጋር እንዴት እናመሳስለዋለን የሚለውን ለማንሳት ነው፡፡ ማስተዋሉ ካለ ተፈጥሮ በአንድም በሌላ መልኩ የምታስተምረን ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ የቡና ጠባይ ትምህርት ይሆነን ዘንድ እነሆ፡፡

    1. ቡና እንዲበቅል ጥላ ይፈልጋል

ቡና ፀሐይ ስለማይችልና ስለሚደርቅ ቡና ሲተከል ጥላ የሚሆነው ተክል(ምሳሌ ሰስፓኒያ) አብሮት ይተከላል፡፡ ያለ ጥላ ቡናን ማሰብ አይቻልም፡፡ አንተም እንደ ቡና የእራስህ የሆነ ነገር ይኖርህና ነገር ግን ያለሌሎች እገዛና ዕርዳታ መቆም የማትችል ዓይነት ሰው ከሆንክ የሌሎችን ዕርዳታና እገዛ መጠየቅን እንደ ስንፍና ወይም አለመቻል አድርገህ አታስበው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አብዛኛዎቻችን ያደግንበት መንገድ ያልገባን ነገር ካለ ጥያቄ እንድንጠይቅ እየተበረታታን ሳይሆን መጠየቅ የዋልጌነትና የዓይን አውጣነት መገለጫ ተደርጎ ነው፡፡ ሰው ካልጠየቀና የሌሎችን እገዛ ማግኘት ካልቻለ የኩሬ ውሃ ሆኖ ነው የሚቀረው ስለዚህ የቡና ጠባይ ይህን በግልጽ ያስረዳናል፡፡

    1. ቡና ብዙ ዝናብና ሙቀት አይፈልግም

ቡና መጠነኛ ዝናብና ሙቀት ነው የሚፈልገው፡፡ ዝናብ ከበዛበት ፍሬ መያዝ አይችልም በአበባነት ብቻ ይቀራል፡፡ ሙቀት ከበዛበት ደግሞ ከነጭራሹኑ ይደርቃል፡፡ አንተም ከሌላው ሊደረግልኝ የሚችላው ድጋፍ ምንድን ነው እስከ የት ድረስ የሚለውን በሚገባ ለይተህ ማወቅ አለብህ፡፡ የሰው ምክርን ብቻ የምትሰማ ከሆነ ፤ በራስህ መወሰን የማትችል ፤ ሁሉም እንደፈለገው የሚመራህ ከሆነ አደጋ አለው፡፡አንተ እራስህን ሳትሆን ሌለውን ሰው ነው የምትመስለው (ግመል ተጭኖ ሰዎች እንደሚመሩት ዓይነት)፡፡ በእራስ ተክለ ሰውነት የሌላውን ሰው ህይወት እንደመኖር ማለት ነው፡፡ ቡና ዝናብ ሲበዛበት አበባ ብቻ ሆኖ እንደሚቀር አንተም የለውጥ የስራ የመነሳሳት ኃይሉ ኖሮህ ትርጉም ባለው ስራ ላይ መቀየር ካልቻክ አበባ እንጂ የሚታይ የሚቆጠር ፍሬ ማፍራት አትችልም፡፡ ስሜትና መነሳሳት ያለ ተግባር በራሱ ብቻ ውጤት ማስገኘት አይችልም፡፡ ቡና ሙቀት ሲበዛበት እንደሚደርቀው ሁሉ ከመጠን ያለፈና ሚዛናዊነት የጎደለው ማንነት ካለህ በአጠቃላይ ሁለንተናህን ሊያጠፋውና ሊያደርቀው ስለሚችል በለዘብተኝነት (flexibility) ነገሮችን ለማጤን በመሞከር እራስህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ፡፡

    1. ቡና ሲያረጅ ይጎነደላል

ቡና እንደማንኛውም ተክል አንዴ ተተክሎ ለዘለአለም ምርት እየሰጠ የሚቀጥል ተክል አይደለም፡፡ መስጠት የሚችለውን ምርት ይሰጥና ለጊዜ እርጅና እጁን ይሰጥና ምርት መስጠት ይቀንሳል ከፍ ሲልም ያቆማል፡፡ እንዲህ ሲሆን ባለቡናው ምርቱን ለማሻሻል ሲል ቡናውን ወገቡ ላይ ይጎነድለዋል፡፡ አዳዲስ ቅርጫፎችን በማውጣት እርጅናውን አውልቆ በመጣል እንደቀድሞው የተሻለ ምርት መስጠት ይጀምራል፡፡ ህይወት ሁልጊዜ ትምህርት ቤት ናት የትናንት ማንነትህና አስተሳሰብህ አውን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይዛመድና እርባና ከሌለው ከላይህ ላይ አውልቀኸው በመጣል ጊዜው የሚጠይቀውን ዕውቀትና አመለካከት መያዝ ግድ ይላል፡፡ ከትናንት ማንነትህ ልምድ በመቅሰም ዛሬን መኖር ፤ ዛሬን እየኖሩ ነገን በተሻለ አተያይና አጋጣሚ ለመጠቀም ዛሬ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡

    1. ቡና በታፈነ መጋዘን ውስጥ የሚቀመጥ ከሆነ ይበላሻል

ቡና ነፍሻማና አየር እንደልቡ ማናፈስ የማይችል መጋዘን ውስጥ የሚከማች ከሆነ ይበላሻል፡፡ ሻጋታ በማውጣ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፡ አንተም ለግላዊ ስብዕናህና ማንነትህ ዕድገት ቦታና ስፍራ ከማይሰጡ ሁኔታዎች ውስጥ እራስህን ማውጣት አለብህ፡፡ ዳግመኛ ከማትመለስበት ልማድና አዋዋል ሰምጠህ እንዳትቀር መጠንቀቅ አለብህ፡፡

    1. ቡና ሲቆላ ማረር የለበትም

ቡና በደንብ እሳት ከገባው ስለሚያር በሚጠጣበት ወቅት ትክክለኛውን ጣዕሙንና ቃናውን ስለሚያጣ አሻሮ አሻሮ ይላል፡፡ አንተም ያለህበት አካባቢ ለዕድገትና ለለውጥ የማይመች ከሆነ ከቻልክ አካባቢህን ለውጥ ካልቻል እራስን ለውጥ ያን ጊዜ መሆን የምትፈልገውን ነገር በሚገባ ታውቀዋለህ፡፡

    1. ቡና ከመቀዳቱ በፊት መስከን አለበት

ያልሰከነ ቡና ድፍርስና አተላ ስለሚሆን እንኳን ጥሩ ጣዕም ሊኖረው ይቅርና ሲጠጣ ለጤና ጠንቅ ነው የሚሆነው (ያቅራል)፡፡ ህይወት ጥድፊያና ሩጫን የምትፈልግ ቢሆንም የሮጡት ቦታ ሁሉ አይደረስምና ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡ ለጸብ ለክርክር መቸኮል የለብህም ፤ ነገሮችን በትዕግስትና በእርጋታ ማሳለፍ በኋላ ከመጸጸት ይጠብቅሃል፡፡ መፍጠን ላለብህ ነገር መፍጠን ትዕግስት ለሚጠይቅ ጉዳይ ደግሞ እንደዚያው ታጋሽ መሆን የብልሆች ምርጫ ነው፡፡ ነገሮችን በቅንነትና በአስተውሎ ከተመለከትነው ከተፈጥሮም ጭምር መማር እንደምንችል ቡናን ምሳሌ አድርገን ተመልክተናል ፡፡

ምንጭ፡-zepsychologist.com