ስትኖር ስትኖር ታመመችና ሞተች፤ ተቀበረች

‹‹ተረት ተረት

‹‹የላም በረት››

‹‹አንዲት ሴትዮ ነበረች››

‹‹እሺ!››

‹‹ስትኖር ስትኖር ታመመችና ሞተች፤ ተቀበረች፤

ይህ የሁላችንም የሕይወት ታሪክ ነው፤››

 

Image result for ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

 

ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በተሰኘው ልብ ወለዱ ላይ በጽሕፈት ዓለም ውስጥ በነበረበት ጊዜ የከተበው ነበር፡፡

‹‹አንዲት ሴትዮ ነበረች›› አለና የእርሷን ሕልፈት ሲያረዳ የቋጨውም ‹‹የሁላችንም የሕይወት ታሪክ ነው፤›› በማለት ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ ሕልፈተ ሕይወቱን ተከትሎ ከአጸደ ሥጋ ተለይቶ ግብአተ መሬቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው ደራሲው ስብሐት፣ በስመ ጥምቀቱ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ኖሮ ኖሮ ታሞ ቢያልፍም፣ ቢቀበርም፣ የብርዕ ትሩፋቱን በተለያዩ መልኮች አስተላልፏል፡፡ ጽልመት ውስጥ የነበሩት ብርሃን ከትቦባቸው ወጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከዕድር፣ ከአነዋር የወጡ አወዛጋቢ ሆነዋል፡፡

አምስት ስድስት ሰባት፣ ትኩሳት፣ ሌቱም አይነጋልኝ፣ ሰባተኛው መልአክ፣ እግረ መንገድ፣ እነሆ ጀግና፣ የፍቅር ሻማዎች፣ ዛዚ (ትርጉም) የተሰኙትን ደረሰ፤ ተረጐመ፤ አሳተመ፡፡ በቀለም አበባ ይዘከርና፡፡

ከሰባ ስድስት ዓመት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት አዲስ አበባን ወርሮ በያዘበት ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ዓድዋ ርባ ገረድ በሚባለው ቦታ የተወለደው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ የመዠመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኰንን ሲከታተል፣ በሥነ ትምህርት (የማስተማር ሙያ) የመዠመርያ ዲግሪውን ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (አዲስ አበባ) አግኝቷል፡፡ ቢኤ ዲግሪው ስንቅ ሆኖት ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ በሚገኘው አሰፋ ወሰን ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት (1953-56) የእንግሊዝኛ መምህር ነበር፡፡ ከማስተማሩም ተሻግሮ በትምህርት ሚኒስቴር ባልደረባ ሆኖ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በሰባት ዓመት ዕድሜው በዕረኝነት የተጀመረው የሥራ ልምዱ ከትምህርትና መምህርነት በኋላ የቀጠለው እስከ ኅልፈቱ የዘለቀበት ጋዜጠኝነቱ ነው፡፡

ከ44 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር የእንግሊዝኛው መጽሔት አዘጋጅነት የተዠመረው ጋዜጠኛነቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ተወዳጅ የነበረችውና፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ሥር ትታተም የነበረችው መነን መጽሔት፣ በይቀጥላልም በኢትዮጵያን ሚረር በአዲስ ሪፖርተር አዘጋጅና ጸሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡

በ1960ዎቹ በነበረችው ቁም ነገር መጽሔት፣ በኋላም በየካቲት፣ የአማርኛና እንግሊዝኛ መጽሔቶች፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹እግረ መንገድ›› (እሑድ) እና ‹‹አንድ ሺሕ አንድ ሌሊት›› (ዓርብ)›› ዐምዶቹ፣ እፎይታ፣ አዲስ አድማስ የብዕር ትሩፋቶቹን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ ስብሐት ከተረኮቹ አንዱ የሆነው ‹‹ሞትና አጋፋሪ እንደሻው›› የብዙዎችን ቀልብ የያዘ፣ ለበዓሉ ግርማ ድርሰትም መነሻ የኾነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይጽፍበት ከነበረው ቁም ነገር መጽሔት ያፈናቀለው ይኸው የአጋፋሪ እንደሻው ተረክ ነው፡፡

የስብሐትን ምልዐተ ታሪክ እስከ ስድሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ድረስ ያለውን ‹‹ማስታወሻ›› በሚል ርእስ ለትውልድ ያስተላለፈው ደራሲና ጋዜጠኛው ዘነበ ወላ ገለታው ይድረሰውና የስብሐትን ጣጣ እንዲህ ከትቦታል፡፡

‹‹ከቁምነገር መጽሔት እንዴተ ተሰናበትክ?››

‹‹በአንድ ቀን ቁራጭ ወረቀት ከሳንሱር ጽሕፈት ቤት አካባቢ ተጻፈልኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የምጽፈው በአጋፋሪ እንደሻው ላይ ነበር፡፡ የደረሰኝ ማስጠንቀቂያ ‹የወዛደሩን ልዕልና የሚያሳይ ካልሆነ ቀልድ ክልክል ነው› ይላል፡፡››

ከትግርኛና አማርኛ ሌላ በእንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ የሚጽፈው፣ ገጣሚም የኾነው ደራሲው ስብሐት፣ ከድርሰቶቹ መካከል ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በፈረንሣይኛ ሲተረጐም፣ አጫጭር ጽሑፎቹ የተካተቱበት ‹‹ዘ ሲድ›› የተሰኘ መጽሐፍም በእንግሊዝኛ ታትሞለታል፡፡

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት የስብሐት ወዳጅ ዘመዶች፣ አድናቂዎች በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሽኝት ሊያደርጉለት ተሰብስበዋል፡፡ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ መሪነት የተካሔደው ጸሎተ ፍትሐት በስመ ጥምቀቱ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ለተሰኘው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ጸሎት እያደረሱ ነው፡፡ ‹‹ከመ መሬት ንሕነ…›› እያሉ በግእዙ ያደርሱታል፡፡

‹‹አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፡፡ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፡፡ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና፡፡››

ከካቴድራሉ አጸድ ውጪ ከቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው አዳራሽ ሥር በሚገኘው ፉካም ቀብሩ ከ12 ሰዓት በኋላ ተፈጸመ፡፡ ስብሐትም አለፈ፤ ስብሐትም ሔደ፡፡

ቀብሩ ላይ የተገኘው ደራሲው ዘነበ ወላ ከ11 ዓመት በፊት በመጋቢት ወር ያሳተመውና ‹‹ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ማስታወሻ›› ብሎ የጠራው ታሪከ ስብሐት፣ በክፍል አንድ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ንኡስ ክፍሉ የተከፈተው ‹‹ሞትን እንቅደመው›› በማለት ነው፡፡

ዘነበ እንዲህ ጻፈ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን [ስብሐት] ‹‹ዘነበ›› [ብሎ ጠራው]

‹‹አቤት ጋሼ?››

‹‹ሞትን እንቅደመው?››

‹‹እሺ! ግን እንዴት?››

‹‹ከማውቀው የማስታውሰውን ሁሉ ልንገርህ!››

‹‹ማለፊያ!››

‹‹የሚጣፈውንም፣ የማይጣፈውንም ነው የምነግርህ››

‹‹እየያዝኩ ነው››

ዘነበና ስብሐት ወጋቸውን ቀጠሉ፤ ወጉም ተጠራቅሞ ባለ345 ገጽ መጽሐፍ ወጣው፡፡ በመጋቢት 1993 ብርሃን ያየው የ‹‹ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ማስታወሻ›› መጽሐፍ በቅብብሎሽ እዚህ ደረሰ፤ ወደፊትም ለትውልደ ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ይፈስሳል፡፡ የተጻፈለት ደራሲው ስብሐት ግን የመጋቢት 13ኛ ወር በሆነችው በየካቲት ተከተተ፡፡ ባሕረሐሳቡ እንደሚለው ዐውዱ ተፈጸመ፡፡

ከመንበረ ጸባዖት ዐውደ ምሕረት ቆሞ ጸሎተ ፍትሐቱን ይከታተል የነበረው የማስታወሻው ደራሲ ዘነበ፣ ከ1993ቱ 65 ዓመተ ስብሐት (ዓ.ስ.) እስከ 2004 ዓ.ም. 76 ዓ.ስ. እስከ ግብአተ ሕንፃ ድረስ የነበረውን የስብሐት ታሪክ አንቀጽ ከነጓዙ ይጽፈው ይሆን? ከሚያውቀው፣ ከሚያስታውሰው፣ ከሚጣፈውም፣ ከማይጣፈውም አወጣጥቶ ያመጣልን፣ ያዘንብልን ይሆን?

ምንጭ፡-.henockyared.com