እናትነት ያልሆነ ምን አለ?፤ የቆምንበት ሁሉ እናት ነው፡፡

‹‹ታሪክን እጠብቃለሁ፤ ግን ሌላ ዓይን እንክፈት››

 

 

‹‹እናትነት ያልሆነ ምን አለ?፤ የቆምንበት ሁሉ እናት ነው፡፡ የተፈጥሮም ሆነ የሰው ልጅ ማሕፀን እናትነትን ያሠርፃል፣ ያወጣል፤›› የሚለውን ኃይለ ቃል ያስተጋባው ሠዓሊውና ካርቱኒስቱ ኤልያስ አረዳ ነው፡፡

ባለፈው ረቡዕ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው በማኩሽ አርት ጋለሪ ለሦስት ቀን የቆየውን ‹‹እናትነት›› የተሰኘውን የሥዕል ዐውደ ርዕይ ባሳየበት ወቅት በአንዱ ሥዕሉ፣ ከመሬት ውስጥ እየወጣች ያለች እንስትን አስመልክቶ የገለጸልን ነው፡፡ ከሠላሳ ሥዕሎቹ ከዘጠና እጅ በላይ በሴቶች ገጽታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የሁሉንም ሥዕሎች አርእስት ‹‹እናትነት›› ብሎታል፡፡

 

ሥዕሎቹ ከባህልና ታሪክ፣ ቅርስና ማንነትን፣ አካባቢና ፍትሕ የተቀዱ ናቸው፡፡ እነርሱኑ ከእናትነት ጋር አወራርሶ አቅርቦታል፡፡

 

‹‹ሰው ዝም ብሎ ዘር ለመቀጠል ብቻ ሳይሆን ማንነትን፣ ሕይወትን፣ ታሪክና ቀጣይነትን አብሮ ይዞት ይወለዳል፤ ከቅድመ አያቶች፣ ከአባት ከእናቱ እየተወለደ እየተቀበለ ይቀጥላል፡፡ የማያባራ የማያቆም ቀጣይነት ያለው ነገር ነው፤›› ብሎም የሚያክለው ሠዓሊ ኤልያስ፣ ባህላዊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ሴቶች አለባበስና አጋጊያጥ የሚያሳይ ነው፡፡ የአርሲን፣ የትግራይን፣ የጎንደርን እንስቶች የሌላውን አካባቢ ሴቶች ጨምሮ በሚወክል መልኩ ከበሬ ጋር አዛምዶ አቅርቦታል፡፡ እንዲህም ያብራራዋል፡፡

 

‹‹በፀጉር አሠራሯ ትግራይ ስትሆን ፀጉሯን ሸብ ማድረጓ አማራ፣ ጌጣጌጧ፣ ጨሌዋና አለባበሷ ኦሮሚያና የተለያዩ አካባቢዎችን ያመላክታል፡፡ ሁሉን አንድ አድርጌ፣ የጋራ የሆነ ነገርን ወስጄ፣ በበሬ ውስጥ ጨምቄ ማሳየቴ እርሻና ገጠር አረንጓዴ አካባቢው  ሁሉ የኢትዮጵያ መሠረት መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡›› 

 

ተመልካቹ ራሱንም እንዲመለከት፣ የራሱም ገጽታ የት ላይ እንዳለ እንዲመለከት ሠዓሊው ፍላጎት አለው፡፡ ‹‹አንዳንድ ሥዕሎች ምን ሐሳብ እንዳላቸው በራሱ መንገድ እንዲተረጉም የራሱንም አንድምታ ማውጣትም አለበት፡፡ ሠዓሊው የተወሰነ ነገር ነው የሚያሳየው፤ ለምሳሌ እኔ አፍንጫና ዓይን ላሳይ እችላለሁ፡፡ ሌላውን ክፍተቱን እየሞላ ማሳየት የርሱ ይሆናል፡፡ በራሱ ግንዛቤ ሥዕሎችን እንዲመለከት ነው፡፡ ከራሱ ጋር እንዲነጋገር ማድረግ ነው፡፡››

 

የሴትን ጀርባ የደብል ቤዝ አንዱ አካል አድርጎ ያቀረበበትና ከሁለት ፍሉት የተሰኘ የሙዚቃ መሣርያ ከሚጫወቱ ሴቶች ጋር ያዛመደበት ሥዕልም አለ፡፡ ‹‹እዚህ ላይ ለኔ ሙዚቃው ሶፍት ስሙዝ ነው፡፡ ሴክሲ የሆነ ሙዚቃ ነው፡፡ የዘሪቱ ከበደ ልስልስ ያለ ዘፈን ስሰማ ይኼን ሥዕል ወዲያው መጣልኝ፣ ዝግ ያለ ነው፡፡ ሙዚቃው ውስጥ ደብል ቤዝ የሆነ መሣርያ አለ፡፡ በደንብ ነው የምሰማት፡፡ ለምን ሴትየዋን ከጀርባ አድርጌ አልሠራሁትም ብዬ ሠራኋት፡፡ የሴትየዋ ቅርፅ ይታያል፡፡ ሰምና ወርቅ ሴት ነች፡፡›› ሥዕሎችህን እንዴት ትገልጻቸዋለህ? ምንስ ትሩፋት አግኝቼበታለሁ ትላለህ? ብለን ላነሣንለትም የሚመልሰውን አላጣም፡፡

 

‹‹ሥዕሎቼ ሕይወትን ከነጉተናዋ የሚገልጹ ናቸው፡፡ ኃላፊውንም፣ መጪውንም የአሁኑንም የሚዳስሱ ናቸውና መዝናኛዬ መደሰቻዬ ሕይወቴ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ምንም የለም፡፡ ሥዕልኮ አብረህ ትኖርበታለህ፡፡››

 

በሌላው ሥዕሉ ደግሞ ኢትዮጵያን የምትወክልና እጇን የዘረጋች እንስት ትታያለች፡፡ ከሥሯ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደርና ሐረር ተደርድረዋል፡፡ ትልቅ የዓይን ብሌን (ጥቁር) ጎልቶም ይታያል፡፡

 

‹‹ይኼ መሬት መሠረት ነው፤ አይረሳም፤ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ያሳያል፡፡ ሌላ በመሠረቱ ላይ እየጨመርክበት ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን እያከልክበት ታሳድገዋለህ፡፡ ይኸንን ነው የማሳየው፡፡ ታሪክን እጠብቃለሁ፡፡ ግን ጥሪዬ ሌላ ዓይን እንክፈት ነው፡፡ በጥቁር ፀሐይ - ጥቁር ብርሃን እጠቀማለሁ፡፡ ጥቁሩ ብርሃኑን ከልሎ ሳይሆን ብርሃኑ ራሱ ጥቁር ነው፤›› በማለትም ያከለው ኤልያስ፣ የልጆች ጨዋታን

‹‹እፉዬ ገላ ያብሽ ገለባ

ሜዳ ነው ብዬ ገደል ስገባ

ገደል ገብቼ ልወጣ ስል›› የሚለውን የልጆች እሽክርክሪት የሚያሳይ ሥዕልም የዐውደ ርዕዩ አካል አድርጎታል፡፡

 

‹‹የምንም ነገር መነሻ እናት ነች፡፡ መሬትንም እናት አገር ብለን ነው የምንጠራው፡፡ ሕይወት የሚጀምረው ከመሬት፣ ከዘር ነው፡፡ ፀሐይ ከሥር ነው፤ ዛፉም ከሥር ነው የሚወጣው፡፡ አፈርና ውኃ ብቻ አይደለም፡፡ ሳይንስ የዋህ ነው፡፡ እኛ ደግሞ በጥበብ እንለውጠዋለን፡፡ በምናብ እናስውበዋለን፡፡››

 

ሠዓሊው የአራት ኪሎ የለውጥ ማዕበልን በሥዕሉ በጽሑፍ (ካፕሽን) ዳስሶታል፡፡ ከባሻ ወልዴ ችሎት እስከ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ ከፓርላማ ፊት ለፊት በምልሰት እስከ ካዛንቺስ ‹‹ፋይፍ ዶርስ›› የነበሩና የፈረሱትን ሴቶች የዘከረበት ነው፡፡ ‹‹ይገባዋል ጠጅ ቤት››፣ ‹‹ዶርዜ ሐይዞ››፣ ‹‹ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ››፣ ‹‹ቼጉቬራ ባር››  በአንድ ባለ ባሬላ ሁሉንም በአንድ ሸክፎ በጥድፊያ እየገፋ ያለበት ሁኔታም የአተኩሮ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

 

አንዱ ተመልካች በሥዕሉ ላይ ‹‹ፋይቭ ዶርስ›› የሚለውን ባየ ጊዜ፣ እነዚያ ካዛንቺስ ቲቶ ቤት ፊት ለፊት በነበሩትና በነርሱ መቃብር ላይ የተሠራውን አዲሱን ራዲሰን ብሉ ሆቴልን ባየ ጊዜ የዚያን ጊዜ ዜማውን እንድናስታውሰው አድርጎናል፡፡

 

‹‹አፈረሱት አሉ ፋይቭ ዶርስን

ያለእናት ያለአባት ያሳደገንን፡፡››

ኤልያስ ከሥዕላዊ ዳሰሳዎቹ ቀዳሚው አብዛኛው ተመልካች ወደ ዐውደ ርዕዩ ሲገባ ያላስተዋለው፣ ግን ሁሉን አይቶ የጥበብ ጓዳውን ለቅቆ ሲወጣ ድንገት የሚገናኘው ፍትሕ ጠቀሱን ሥዕል ነው፡፡

 

ባልቴቷ በንዴት ጦፈዋል፡፡ ከፍትሕ አደባባይ ከችሎት ሳጥን ውስጥ ገብተው ተደግፈዋል፡፡ ንዴታቸው ብሎም እሮሮአቸው ከጭንቅላታቸውም፣ ከዓይናቸውም ውስጥ ወጥቶ ይታያል፡፡ የሕግ ያለህ! እያሉ ለተከበረው ፍርድ ቤት አቤቱታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም፡፡ የፍትሕ ወንበሩ ባዶ ነውና፡፡ ዳኛም አልተቀመጠበትም፡፡

 

ይኸንን ሥዕል እያየሁ የማኩሽን ጋለሪ ለቅቄ ስወጣ የሴትየዋ ገጽታ ግን ሊለየኝ አልቻለም፡፡ የነፍስ ኄር (the late) ጥላሁን ገሠሠ ታላቅ ዜማም ታወሰኝ፡፡

‹‹ጩኸቴን ብትሰሙ

ይኸው አቤት አቤት እላለሁ

በደል ደርሶብኝ እጮሃለሁ፡፡››

ምንጭ፡- 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ