የአለማችን ረጃጅም ጥፍሮች ባለቤት ከ1952 ወዲህ ጥፍራቸውን እንዳልቆረጡ ይ

የአለማችን ረጃጅም ጥፍሮች ባለቤት ከ1952 ወዲህ ጥፍራቸውን እንዳልቆረጡ ይናገራሉ

 

long_Nail2.jpg

 

የአለማችን ረጃጅም ጥፍሮች ባለቤት የሆኑት ህንዳዊ ከ1952 ወዲህ የእጃቸውን ጥፍሮች እንዳልቆረጧቸው ተናግረዋል።

ከ16 አመታቸው ጀምሮ ጥፍራቸውን መቁረጥ ማቆማቸውን የገለጹት የ78 አመቱ አዛውንት፥ በ2016 የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ መጽሃፍ ውስጥ ተካተዋል።

ሺሪድሃር ቺላል የተባሉት ህንዳዊ  የግራ እጃቸውን ጥፍሮች ማሳደግ የጀመሩት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ ነበር።

ሺሪድሃር ጥፍራቸውን ለማሳደግ ምክንያት የሆናቸውን ሲገልጹም፥ “በልጅነቴ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ጓደኛዬ የአስተማሪያችን ረጅም ጥፍር በመስበሩ በሀይለኛው ደበደበን፤ ጥፍሩ ስለተቆረጠ ብቻ ለምን እንደዚህ እንደመታን ስንጠይቀውም “እናንተ ጥፍራችሁን ካላሳደጋችሁ አይገባችሁም” አሉን ብለዋል።

ከዚያ በኋላም ጥፍራችንን ካላሳደግን አስተማሪያችን የተሰማውን ስሜት ማወቅ አንችልም በሚል ጉጉት ጥፍሬን ማሳደግ ጀመርኩ ይላሉ አዛውንቱ።

በአሁኑ ወቅት የሺሪድሃር ጥፍሮች አጠቃላይ ርዝመት 909 ነጥብ 6 ሴንቲ ሜትር ወይም ከ9 ሜትር በላይ ነው።

የአውራ ጣታቸው ጥፍር ከሁሉም ረጅሙ ሲሆን፥ 2 ሜትር ይረዝማል፤ የመሃል ጣታቸው ደግሞ በ1 ነጥብ 86 ሜትር ይከተላል።

የቀለበት ጣታቸው 1 ነጥብ 81 ሜትር፣ የማርያም ጣታቸው እና  የአመልካች ጣታቸው ጥፍሮች ደግሞ 1 ነጥብ 79 ሜትር እና 1 ነጥብ 64 ሜትር እንደሚረዝሙ ተገልጿል።

 

የአስተማሪያቸውን ስሜት ለማወቅ በሚል ጥፍራቸውን ማሳደግ የጀመሩት ሺሪድሃር ከቤተሰቦቻቸውና ከመምህራን እያደር ተቃውሞ ቢበረታባቸውም በአቋማቸው መጽናታቸውን ይናገራሉ።

ልብስ ማጠብ እና ስራ መፈለግ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር የሚገልጹት ሺሪድሃር፥ በተለይም የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት ተቸግሬ ነበር ይላሉ።

ከ10 እስከ 12 እንስቶች ሙከራ በኋላ በ29 አመታቸው ትዳር እንደመሰረቱም ነው የተናገሩት።

የግራ እጃቸውን ጥፍር ብቻ ለማሳደግ መወሰናቸውም በቀኝ እጃቸው የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

ሺሪድሃር ለ63 አመታት ያልቆረጧቸው ረጃጅም ጥፍሮቻቸውን ቆርጠው በሙዚየም ለማስቀመጥ ማቀዳቸውንም ዴይሊ ሜል በዘገባው አመልክቷል።

 

  

ምንጭ፡- FBC