የድድ ችግር በማንኛዉም ሰዉ ላይ ሊከሰት የሚችል ነዉ::
የድድ እንፌክሽን Gingivitis
ጄንጅቫይትስ (የድድ እንፌክሽን) ብዙ ጊዜ የሚከሰት የድድ/የጥርስ ዙሪያ ላይ ህመም ሲሆን መቆጥቆጥ፣ ቅላትና እብጠት በድድዎ ላይ እንዲከሰት ያደርጋል:: ብዙዉን ጊዜ ህመሙ መጠነኛ የሆነ ምልክት ስለሆነ ያለዉ ታማሚዉ ሳያስተዉለዉ ሊያልፍ ይችላል::
የህመሙ ምልክቶች፡ ጤናማ ድድ ጠንካራና ቀላ ያለ ሮዝ ቀለም ያለዉ ሲሆን የድድ ላይ ህመም ሲከሰት የሚከተሉትን ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል:: እነርሱም
• የድድ እብጠት
• ልልና የተነፋ ድድ
• አንዳንዴ ሲነካ ህመም መኖር
• ጥርስዎን በሚፍቁበት/በሚቦርሹበት ወቅት በቀላሉ መድማት
• የድድዎ መልክ መቀየር(ከጤናማ ቀይ ወደ ደበዘዘ ቀይ)
• መጥፎ የአፍ ጠረን መከሰት ናቸዉ
የህመሙ ምክንያቶች
ጄንጅቫይትስ በብዛት የሚከሰተዉ የአፍ ዉስጥ ንፅህናን በደንብ በማይጠብቁና በዚህ የተነሳ በድድና ጥርስ ላይ የሚጋገር ነገር/ plaque/ እንዲፈጠር እድል የሚፈጥሩት ሰዎች ላይ ነዉ:: ይህ የተጋገረዉ ነገር በዐይን የማይታዩ ባክቴሪያዎችን የያዘ ነዉ::
ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
የድድ ችግር በማንኛዉም ሰዉ ላይ ሊከሰት የሚችል ነዉ:: ነገር ግን ተጋላጭነትዎን ከሚጨምሩ ነገሮች ዉስጥ
• የአፍ ጤንነታቸዉን/ ንፅህናቸዉን በደንብ በማይጠብቁ
• ሲጋራ በሚያጨሱ ሰዎች ላይ • የስኳር ህመም
• በእርጅና እድሜ ወቅት
• መድሃኒቶች
• የአፍ ድርቀት
• የሆርሞን ለዉጥ( በተለይ በሴቶች ላይ እርግዝና፣ በወር አበባና የእርግዝና መከላከያ እንክብል በሚወስዱበት ወቅት)
• ጥሩ አመጋገብ ከሌለዎ እና
• አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ከሆነ ነዉ::
ሊደረግ የሚችል ህክምና
ለህመሙ የሚደረግ ህክምና የህመም ምልክቶቹን ከመቀነስ ባሻገር ህመሙ ወደከፋ ደረጃ እንዳይሄድና የጥርስ መዉለቅን ሊከላከል ይችላል:: ዉጤታማ ህክምና ለማግኘት የባለሙያ ክትትልና ከህመሙ በኃላ የአፍ ዉስጥ ንፅህናን መጠበቅ ያስፈልጋል::
የቤት ዉስጥ ህክምናና የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥ
• የጥርስ ህክምና ባለሙያዉ በሚያዘዉ መሰረት መደበኛ የሆነ የጥርስ እጥበት ማካሄድ
• ለስለስ ያለ የጥርስ ቡርሽ መጠቀምና ቢያንስ በየሦስትና አራት ወራት መቀየር
• በቀን ሁለቴ አሊያም ከእያንዳንዱ ምግብ መርሃግብር በኃላ አፍዎን ማፅዳት
• የጥርስ ህክምና ባለሙያዎ ካዘዘልዎ የጥርስ ማጠቢያ አንቲሴፕቲክ መጠቀም
• በጥርስ መካከል ለማፅዳት ተብለዉ የተዘጋጁ የጥርስ መጎርጎሩያ/ዴንታል ፒክ መጠቀም::
source-zehabesha